2016 ኖቬምበር 18, ዓርብ

እኛና የፈጠረን



እኛና የፈጠረን
በእርግጥ ዛሬ ዛሬ በእኛና በፈጠረን መካከል እልቆ ቢስ የሆነ ልዩነት ተፈጥሯል። ታዲያ ይህ ልዩነት ደግሞ አርፎ አልተቀመጠም። ይልቁንም ሁለታችን በጣም እንድንለያይና እንድንራራቅ ከድንጋይም በላይ ተራራ ለመፈንቀል እየሮጠ ይገኛል እንጅ። ምንም እንኳ አስተውለነው ባናውቅም ድሮ እኛና ፈጣሪ በጣም ወዳጆች ነበርን። ለነገሩ ዛሬ እኮ “ነበር’ን” ስለማንወድ ከነበርን ይልቅ “ነን” ስለሚመቸን እውነታን ለመቀበል እየተቸገርን ነው። ነበር ያለበት ሁሉ ተረት ተረት ነው የሚመስለን። ነበር ሁሉ ጠላት ነው የሚመስለን። ነበር ስላለበት ብቻ ስለ ታላቁ አያታችን እንኳ ሲወራ ውስጣችን በጥላቻ የሚንቦገቦግ ብዙዎች ነን። ነበር ስላለበት ብቻ የተወለድንበትን ቀን ራሱ ማስታወስ አንፈልግም። ምክንያቱም ወላጆቻችን ስለ ልደታችን ሲነግሩን “አንተ የተወለድከው ልክ የዛሬ 21 አመት ጥር 21 ቀን ነበር። አንተ ስትወለድ እኔና ባለቤቴ በጣም በደስታ ተመልተን ነበር። ስለትም አስገብተን ነበር ወዘተረፈ” እያሉ ንግግራቸውውን በነበር እየቋጩ ስለሚነግሩን እነርሱ እያወሩን ላለመስማት ፌስ ቡክ እንጠቀማለን። ከነበር ጋር ተጣልተን ስላለፈ ታሪካችን ሳናውቅ ማንነታችንን ሳንረዳ የዕድሜያችንን ግማሹን አሳልፈናል። ነበርን ራሱን በነበር እያለፍን በራሳችን ላይ እየቀለድን ዛሬ ላይ ደርሰናል። ነበርን ስለጠላን ከቁሳቁስ በስተቀር ለልጆቻችን የምናወርሰው አንዳች መልካም ነገር አጥተናል። ስለራሳችን ታሪክ እንኳን ልንነግራቸው አንፈልግም። የህይዎት ተሞክሯችንን ልናካፍላቸው አልቻልንም። ከስተታችን ተምረው በጥንካሬያችን ጠንክረው ነገ ላይ ከእኛ የተሻለ ህይወት እንዲኖራቸው እያደርግን አይደለም። ምናልባት ዛሬ ያወረስናቸው ቁሳቁስ ነገ በሆነ ምክንያት ቢጠፋባቸው ሰርተው መተካት እንዲችሉ እያደረግናቸው አይደለም። የራሳችንን ልጆች ለከፋ ችግር እየዳረግናቸው ነው። እነርሱም ያወረስናቸውን ነገር ጨርሰው ለልጆቻቸው ምን እንደሚያወርሱ እርሱ የፈጠረን ይወቀው። በአጠቃላይ በዚህ ባለንበት ዘመን በእኛና በልጆቻችን መካከል ያለው ልዩነት ከጊዜ ወደጊዜ እየሰፋ በእኛና በፈጠረን መካከል ያለውን እያከለ ነው። ይሄ ደግሞ ከቀጠለ ልጅና ወላጅ ባዕድ መባላቸው አይቀርም። ነበርን ላለማውራት ስለኛ እንድያውቁ አላደረግንማ። ለነገሩ ነበርን ባንጠላ ነበር የሚገርመው። በሀገራችን ያሉ መገናኛዎች (ንፋሰ ድምፅና ትዕይንተ መስኮት) በሙሉ የሚያስተምሩን የነበርን መጥፎ ጎን ብቻ ነው። የሚያስተምሩን በነበር ውስጥ ከጀግንነት ይልቅ ጅልነት፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ፣ ከውለታ ይልቅ በደል፣ ከሀገር ወዳድነት ይልቅ ባንዳነት፣ ከከለላነት ይልቅ ጨፍጫፊነት፣ ከጡት አጥቢነት ይልቅ ጡት ቆራጭነት፣ ከፍትሀዊነት ይልቅ አድሏዊነት እንዳለ ብቻ ነው። እኛም እውነታው ከነገሩን በተቃራኒው እንደሆነ አላወቅንም። ምንም ሳንደክም ያሉንን ተቀበልናቸው። ይሄ ደግሞ ለነበር ያለንን ፍቅር በማጥፋት የፈጠረንን ልክ እንደ አያታችን ታሪክ እንድንረሳው አድርጎናል።
          የፈጠረን ራሱ እንዳለው እኛና እርሱ በጣም እንዋደድ ነበር። የምንኖረውም እርሱ ከፍታው ላይ ቢሆንም እንኳ አንድ ሰፈር ውስጥ ነበር። ታዲያ ምንያደርጋል እኛው በጥጋባችን ከሰፈሩ ተባረርን። ካስታወሳችሁ ያኔ ርሀብ፣ ችግር፣ቸነፈር፣ህመም፣ በሽታ፣ ማጣት፣ መጠማት፣ እርዛት፣ መከፋት ማዘንና መተከዝ የሚባሉ ቃላት በቋንቋችን ውስጥ እንኳን አልነበሩም። እነዚህ ቃላት ከሰፈራችን ከተባረርን በኋላ በቋንቋችን ውስጥ ዘልቀው የገቡ መጤዎች ይሁኑ እንጅ ዛሬ የዕት ተዕለት መግባቢያችን ናቸው። እንዴውም እነርሱ ባይኖሩ ቋንቋችን ምሉዕ ሆኖ ያግባባናል ለማለት ያስቸግራል። ያኔ እዚያው እያለን በብቸኝነት ስንጠቀምባቸው የነበሩት ቃላትን ማለትም ደስታ፣ ጥጋብ፣ እርካታ፣ ጤናና ሌሎችን ያለእነዚህ ቃላት እርዳታ ማውራት አንችልም። ስሜታችንን፣ ሀሳባችንን፣ ምኞታችንንና እንቅስቃሴያችንን ለመግለጽ እነርሱ የግድ ያስፈልጉናል። እናም ያኔ እኛና የፈጠረን ፍቅራችን በቃላት የማይገለጽ ነበር። በጣም ስለሚወደን ከመኖሪያው እየመጣ ደህንነታችንን ይጠይቀናል። እኛም በጣም ስለሚናፍቀን ሁልጊዜ እንጠራው ነበር። ስንጠራውም ፈጥኖ መጥቶ የጎደለንንና የሚያስፈልገንን ይጠይቀናል። በእርግጥ እኛ እንድንጠይቅ ፈልጎ እንጅ ምን እንደምንፈልግ እርሱ ጠንቅቆ  ያውቃል። ካልረሳችሁት እርሱ በጣም የሚያስፈራ ግርማ ሞገስ ነበረው። አሁንም አለው። ቸር ስለሆነ እንዳንቀና ከግርማሞገሱ ሰጥቶን ነበር። እኛ ግን በጣም ስግብግቦች ነን። የርሱን ሞገስ ለማግኘት ስንሮጥ ነው እኮ ጥፋት አጥፍተን ክብራችንንና ሞገሳችንን ተቀምተን ከሰፈራችን የተባረርነው። እንዴውም ርኁሩኅ ሆኖ ራርቶልን እንጅ እንደጥፋታችንማ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ አንደርስም። እርሱ ግን እንደኛ አይደለም። አቤት የኛ በደል እኮ ብዛቱ።
          የፈጠረን እርሱ እንዳለው መጀመሪያ ሲፈጥረን አዳም ብሎ ሰየመን። እኛ ደግሞ ዛሬ ስማችንን ቀይረነዋል። ምን ስማችንን ብቻ ግብራችን ራሱ ተቀይሯል። የፈጠረንም በጣም ግራ ገብቶታል። ይጠራናል ግን አንሰማውም። ይመክረናል አንቀበለውም። ከፊታችን ቆሟል አናየውም። ነፃ አርጎናል እኛ ግን ነፃነታችንን አጥተን በጣም ተጨናንቀናል። ሰው ብሎ ስም ሰጥቶን እያለ እኛ ሌላ ስም ፍለጋ እንኳትናለን። እንስሳ ተብለን ለመጠራት የማናደርገው ጥረት የለም። ለኛ የሰጠንን ጸጋ ትተን የእንስሳትን ስራ እየሰራን ነው። ግን ይሄ ነገር ይታወቀናል? የፈጠረን በጣም አዝኗል። ወዮልን። ለነገሩ ምክር ሰልችቶናል። ከተፈጠርን ጀምሮ ምክር ትናንት ምክር ዛሬ ምክር ነገ ምክር እንዴ ከምክር ውጪ ሌላ ነገር የለም? በቃ ሰለቸና። መመከር አንፈልግም። ተመክረን ተመክረን ጠግበናል። ምክር አስጠልቶን አይደለም እንዴ ከምንወደው አባታችን የተጣላነው? በቃ አትምከሩን አንፈልግም።
እናስተውል።
ዳንኤል ገብረ ማርያም

1 አስተያየት:

  1. ለሙከራ የተለጠፈ ስለሆነ እርስዎ አስተካክለው ያንብቡት። ለወደፊት በአዳዲስ ጦማሮችና ሀሳቦች እመጣለሁ።

    ምላሽ ይስጡሰርዝ